Ethiopian Freight Forwarders and Shipping Agents Association

ኢትዮጵያ ቀደም ሲል የነበረውን በበርበራ ወደብ አልምቶ የመጠቀም መብቷ እንደማይነካባት በሶማሊላንድ ፕሬዚደንት በኩል ይፋ ሆኗል፡፡

የበርበራን ወደብ አልምቶ ለመጠቀም ድርሻ ያላት ኢትዮጵያ ዳግም ስምምነቷን ከሶማሊላንድ ጋር አፅንታለች፡፡

ስምምነቱም ወደውል እንደሚቀየር የምሥራብ የሬድዮ መጽሔት ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸውና የድርድሩን ሒደት ከሚሳተፉ የመንግሥት ሹም መረጃ አግኝቷል፡፡

ከትናንት በስቲያ ወደ ሶማሊላንድ ከተማ ሐርጌሳ የኢትዮጵያ ልዑክ ማቅናቱንና የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ እንዲሁም በአምባሳደር ሬድዋን ሁሴን የተመራ የልዑካን ቡድን ከሶማሊላንድ ፕሬዚደንት ሙሴ ቢሂ አብዲ ጋር መነጋገሩን የሶማሊላንድ ብሔራዊ ጣቢያ ተናግሯል፡፡

ኢትዮጵያ የበርበራን ወደብ ለማልማት ከሶማሊላንድና ከዲፒ ወርልድ ኩባንያ ጋር የጋራ ስምምነት እንደነበራት ይታወቃል፡፡ በዚህ ስምምነት 19 በመቶ የወደቡና ድርሻ የምትይዝ ሲሆን ባለፈው ወር ክፍያ ባለማጠናቀቋ ድርሻዋ ተነጥቋል ሲሉ የሶማሊላንድ የገንዘብ ሚኒስቴር መናገራቸው ይታወሳል፡፡

ይህን የተናገሩት ሚኒስትር ጭምር በተገኙበት ፕሬዚደንታዊ የእራት ግብዣ የተደረገለት የኢትዮጵያ ልዑክ ስምምነቱ ባለበት አንደሚቀጥል ማስተማመኛ ተሰጥቶታል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ፕሬዚደንት ሙሴ ቢሂ አብዲና አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በሁለቱ ሃገሮች የንግድ እንቅስቃሴና የበርበራ ወደብን በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡

ስምምነቱ ሁለቱንም ሃገሮች አልፎ ተርፎም የአፍሪካን ቀንድ በእጅጉ የሚጠቀም ስለመሆኑ የሶማሊላንድ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በትዊተር ገጹ ላይ አስፍሯል፡፡

Share on

Share on facebook
Facebook
Share on twitter
Twitter
Share on linkedin
LinkedIn
Share on telegram
Telegram
Share on whatsapp
WhatsApp
Share on email
Email